የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከፌዴራልና ከክልል ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ህዳር 6 እና 7 ቀን 2012 ዓም የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስትቲዩት አካሂዷል።

በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የመክፈቻ ንግግር በይፋ በተከፈተው የባለድርሻ አካላት መድረክ ላይ በቀዳሚነት ቀርቦ የነበረው የዳያስፖራ መረጃዎች በዘመናዊና በተደራጀ መልኩ የመያዝ አስፈላጊት ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዳያስፖራ መረጃ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ክፍተቶች የቀረቡበት ነበር፡፡ በሁለተኛው አጀንዳም የኤጀንሲው፣ የክልል ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች እንዲሁም የዳያስፖራ ማህበራት የበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበውበታል፡፡ በዚህም ወቅት በኤጀንሲውም ሆነ በባለድርሻ አካላት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትና ያጋጠሙ ችግሮች በስፋት ተዳሰዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎችም በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የኤጀንሲው አመራሮችም ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሾችንና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ከተነሱት ዋና ዋና ሃሳቦች መካከልም በዘመናዊ መልኩ ሊደራጁ ስለታሰቡት መረጃዎች አይነትና ቅድሚያ ስለተሰጣቸው የመረጃ አይነቶች፣የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ላይ የሚገጥሙ ማነቆዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመፍታት ኤጀንሲው ስለሄደበት ርቀት፣በክልል ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች መካከል የሚታየው የአደረጃጀት ልዩነትና የአቅም ውስንነት ስለሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲሁም በሃገር ውስጥ የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበራት አደረጃጀቶች ጠንካራ የሚሆንበት ሁኔታን የተመለከቱት ጥቂቶቹ ነበሩ።
የምክክር መድረኩ ከተጠናቀቀ በኋላ ተሳታፊዎች ወደ ታላቁ ቤተ መንግስት በማምራት የአንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል።