አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት እና ትግበራ ላይ ውይይት ተደረገ

ክቡር የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበብራስል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በመገኘት በአዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት እና ትግበራ ላይ ከዲፕሎማቶች ጋር ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይተዋል።በዚህ ወቀት በሀገሪቱ በየደረጃው ባለው የትምህርት እርከን እየገጠመ ስላለው የትምህርት ጥራት መጓደል የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።በአጠቃላይ ትምህርትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወደፊት አደረጃጀትን አስመልክቶ በቀረበዉ ሰነድ ላይ ህብረተሰቡ በስፋት ተወያይቶ ጠቃሚ ሃሳቦችና አስተያየቶች ተሰብስበው መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥልቅ ጥናት ተደርጎበት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አካትቶ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ የቬትናምንና ማሌዥያን እንዲሁም የሌሎችን ሃገሮች ልምድ በማካተት የተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታው ለሚቀጥሉት አመታት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ፍኖተ ካርታው በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሚገባ ተማሪም መጀመርያውን አንድ አመት ሙሉ ሃገሪቱን ታሪክ፣ ባህልና መልክአምድር በማጥናትና በመማር ግብረገብነትን ያዳበረ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡
የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው በአገሪቱ የሚሰጠው ትምህርት እውቀት ብቻ ሳይሆን ተግባርን ያማከለ እንዲሁም አገር በቀል እውቀትና አስፈላጊውን ክህሎት ያካተተ እንዲሆን ለማስቻል ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።
በእዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ ከሌሎች በተለያዩ ሀገሮች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ጋር ለመወያየት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ውይይቱ ስለፍኖተ ካርታው ግንዛቤ ለመፍጠር ከማገዙ ባሻገር ለልማት አጋሮች ስለ ፍኖተ ካርታው ማስረዳትና ድጋፍ ማስገኘት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም በጉዳዩ ላይ ከዲፕሎማቶቹ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።