7ኛው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውሃ ጉዳይ የሚኒስትሮች ስብሰባ ተጀመረ

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ የሚመክረው የመጨረሻው የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የቴክኒክ ስብሰባ ዛሬ ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲሰ አበባ መካሄድ ተጀምሯል፡፡

የዛሬው ስብሰባ በዋናነት የግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በሚመለከት ውይይት ያደርጋል፡፡

በስብሰባው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክቡር የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ የአባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ድህነትን ማጥፊያ እና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ስብሰባው በግድቡ ሙሌት እና የውኃ አለቃቅ ዙሪያ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ተስፋቸውን በመጠቆም ሚኒስትሮቹ በሶስቱ ሀገራት ዘንድ በጉጉት ለሚጠብቁት ህዝቦች መልካም ዜና ለማብሰር ውይይቱን በሰከነና በመግባባት መንፈስ በማካሄድ መቋጨት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ ለዚሁም መሠረቱ የመሪዎች መግለጫ፣ የወንዙን ውኃ ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ባለማድረስ መርህ እንደሆነም ዶ/ር ስለሽ ጠቁመዋል፡፡

የግብጽ እና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮችም በስብሰባው መክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በትብብር መንፈስ በአጀንዳዎቹ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግና የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በስብሰባው የዓለም ባንክ እና የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተዋል፡፡