በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ ላይ ለሁለት ቀናት በአደስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የውሃ ሚኒስትሮች ቴክኒካል ስብሰባ ዛሬ ታህስስ 30 ቀን 2012 ዓም ተጠናቋል፡፡
ስብሰባው የውሃ ሚኒስትሮቹ እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 06 ቀን 2019 ወዲህ የተደረገ አራተኛ የሚኒስትሮች ቴክኒካል ስብሰባ ነው፡፡ ስብሰባዎቹ የሶስቱ ሀገራት መሪዎች እ.ኤ.አ 10 ፌብሩዋሪ 2019 አዲስ አበባ ባካሄዱት ስብሰባ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው የቴክኒክ ምክክሮችን በማድረግ በህዳሴ ግድብ ሙሌት እና አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ አማራጭ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ በሰጡት መመሪያ መሰረት የተከናወነ የመጨረሻው ስብሰባ ነው፡፡
በስብሳባው የዝቅተኛ ውሃ አለቃቅ መጠን እና የድርቅ እና የተራዘመ ድርቅ ወቅት የሚኖረውን ትብብር ጨምሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅን የሚመለከቱ ቀሪ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ስብሰባው ያለስምምነት ተጠናቋል፡፡
ኢትዮጵያ ወንዙ በግድቡ ስፍራ እንደሚኖረው ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከ4 – 7 አመታትን በሚወስድ የሙሌት ደረጃ ግድቡን ለመሙላት፣ በሙሌት እንዲሁም ግድቡ ሙሌት አጠናቆ ስራ ከጀመረ በኋላም ድርቅ ከተከሰተ የማቃለያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሃሳቦችን አቅርባለች፡፡
እነዚህ ሃሳቦች የታችኛው ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እዳይደርስ የሚያስችሉ እንዲሁም ግብጽ እና ሱዳን ያቀረቧቸውን ሃሳቦች ያካተቱ ቢሆንም የግብጽ ወገን ያቀረብኩት ሃሳብ በሙሉ ተግባራዊ ካልሆነ የሚል አቋሙን ሳይንሳዊ ማስረጃ ቢቀርብለትም ሊቀበል ባለመቻሉ የቴክኒክ ውይይቱ ያለስምምነት ተጠናቋል፡፡
የግብጽ ወገን በዚህ ስብሰባ ያቀረበው ሃሳብ ኢትዮጵያ ከ12 – 21 አመታት ውስጥ ግድቡን እንድትሞላ እንዲሁም ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የግድብ አሞላል እና አለቃቀቅ ዕቅድ ድርቅን ከግምት ያስገባ ሆኖ እያለ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት የሚል ሃሳብ መነሳቱ ተገቢ አይደለም፡፡ በተጨማሪም የግብጽ ሃሳብ በናይል ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዳለ የሚገምት እና ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት በላይ በጥቁር አባይ ወንዝ ላይ የሰራቻቸው የውሃ ልማት ስራዎች እንዳልተገነቡ የሚቆጥር ወይም እውቅና የሚነፍግ ነው፡፡
የግብጽ ሃሳብ ግብጽ በተፋሰሱ ላይ አለኝ የምትለውን የብቸኛ የውሃ ባለቤትነት ለማስጠበቅ የሚጥር ነው፡፡ ይህ አቋም በርትዕ እና ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ የውሃ አጠቃቀም እና በትብብር መስራት መርሆዎችን የሚጥስ ነው፡፡ እነዚህ እንዲሁም ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መሰረታዊ መርህ ግብጽ፣ ሱዳን እና ሀገራችን በመሪዎች ደረጃ መጋቢት 2007 ዓ.ም ላይ በካርቱም በፈረሙት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት ውስጥ የተካተቱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የአባይ/ናይል ወንዝ አጠቃቀም ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን የማስከበርና የነባሩን እንዲሁም የመጪውን ትውልዶች የመጠቀም መብት የማረጋገጥ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥልበታለች፡፡ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ለተፈረሙ እና አባል ላልሆነችባቸው የቅኝ ግዛት እና ድህረ ቅኝ ግዛት ኢፍትሐዊ እና አግላይ እንዲሁም ለናይል ወንዝ 77 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለምታዋጣው ኢትዮጵያ 0 ድርሻ ለሚሰጡ “ውሎች” እውቅና እንድትሰጥ የሚደረጉ ሙከራዎችን አትቀበልም፡፡ በተጨማሪም ሀገራችን ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በምታደርገው ውይይት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትብብር እና የጋራ ልማት ምሳሌ እንዲሆን በወንድማማችነት፣ በቅን ልቦና እና በመተባበር መንፈስ ጥረቷን ትቀጥላለች፡፡
በቀጣይ የውሃ ሚኒስትሮቹ የተስማሙባቸው እና ልዩነት የተመዘገበባቸው ጉዳዮች ተለይተው ለመሪዎች የሚቀርቡ ሲሆን መሪዎች ስለቀጣይ እርምጃ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ የሚመለከቱ ሁሉም ቴክኒካዊ ጉዳዮች በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ሀገራቱ ሙሌት እና አለቃቀቅን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ መቀራረብ አሳይተዋል፡፡ ሁሉም ሀገራቱ በውይይቱ የሚያደርጉት ተሳትፎ በቀናነት እና የትብብር መንፈስ ከተከናወነ የሚኒስትሮች ስብሰባዎቹ ሀገራቱ በራሳቸው መካከል በሚደረግ ውይይት ስምምነት ለመድረስ ያላቸውን እድሎች ያሳየ መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች፡፡
የውሃ ሚኒስትሮቹ እ.ኤ.አ ጃኑዋሪ 13 ቀን 2020 በዋሽንግተን ዲሲ የሚገናኙ ሲሆን ስብሰባው እስካሁን የተደረጉ የቴክኒክ ምክክርች ሂደት የሚገመገምበት ብቻ ይሆናል፡፡