ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተለያዩ አገራት ልዩ መልዕክተኞችን አነጋገሩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን ዛሬ ጥር 28 ቀን 2012 ዓም የአየርላንድ መንግስት የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕከተኛ አምባሳደር ኬኔት ቶምሶን እና የፍልስጥኤም አስተዳደር የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛና የሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑት አምባሳደር ዶ/ር ናስሪ አቡጃሽ ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአየርላንድ መንግስት ልዩ መልዕከተኛ ጋር በነበራቸው ውይይት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። በኢትጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ በተመለከተ ክቡር አቶ ገዱ ገለጻ አድርገዋል። አየርላንድ በኢትዮጵያ የምታካሂደውን የልማት ፕሮግራም አጠናክራ እንድትቀጥል አንዲሁም የአየርላንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ክቡር አቶ ገዱ በዚህ ወቅት ጠይቀዋል።

የአየርላንድ መንግስት ልዩ መልዕከተኛ አምባሳደር ኬኔት ቶምሶን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለቀጠናው እና ለአካባቢው ሰላም የምታደርገውን እንቅስቃሴ አየርላንድ ታደንቃለች ብለዋል። አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ የቆየ ግንነኙት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደር ኬኔት ገልጸዋል። የአየርላንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ ሁኔታ ኢንቨስት እንዲያደጉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ልዩ መልዕክተኛው አረጋግጠዋል።

በተያያዘ ዜና ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የፍልስጥኤም አስተዳደር ልዩ መልዕክተኛ እና የስራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን አምባሳደር ዶ/ር ናስሪ አቡጃሽ ጋር መክረዋል። ክቡር አቶ ገዱ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እያካሄዱ ያሉትን ውይይት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
የፍልስጥኤም መንግስት ልዩ መልዕክተኛ እና የሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ዶ/ር ናስሪ አቡጃሽ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፈን እያደረገች ያለውን የጎላ ሚና አድንቀዋል። በታላቁ የህዳሴው ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ እየተካሄደ ያለው ውይይት በሰላም እንደሚጠናቀቅ እምነታቸው መሆኑንም ገለጸዋል። ፍልስጥኤም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል አየሰራች ነውም ብለዋል።