የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ ይፋ ሆነ

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይፋ አደረገ።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ረቂቅ አዋጅ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅጽደቁ ይታወቃል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዋጁን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ንኡስ ቁጥር 4 መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚህም መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ዝርዝር በሚመለከት ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል።

ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ከፍሎች ያሉት ሲሆን ይሄውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግደታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑ ተጠቅሷል።

ክልከላን በሚመለከት ማንኛውም ሃይማኖታዊ ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከ4 ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል ናቸው።

አራት ሰዎችም ቢሆኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መሆን እንዳለበት አቃቤ ህጓ አብራርተዋል።

ቀብርና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል።

ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም ጥየቃ ለሚሄዱ ሰዎች የማይፈቀድ መሆኑ ተገልጿል።

በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መሆኑን አስረድተዋል።

በድንበር አካባቢ ከካርጎ፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ ተደርገዋል።

የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም መጨመር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል።

ሰራተኞችን መቀነስና የስራ ቅጥር ውል ማቋረጥም መከልከሉን ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል።

በዚህ ደንብ መሰረት ተማሪዎችና መምህራን በኦን ላይን ካልሆነ በአካል እንዲገናኙ አይፈቀድም።

ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የህፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።

በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ ነው፡፡