በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የባቡር ትምህርት ማእከል ሊቋቋም ነው

Ethio Railway School

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 29 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የባቡር ትምህርት ማእከል ሊቋቋም ነው።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ጌታቸው በትሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ፤ የትምህርት ማእከሉ በመጭው አመት ስራ ይጀምራል።

ተቋሙ ወደ ቻይናዋ ቲያንጅን የባቡር ትምህርት ማእከል አቅንተው ስልጠና በመውሰድ ላይ ያሉ ባለሞያዎችን በአሰልጣኝነት የሚጠቀም ሲሆን የባቡር ሾፌርነት ፣ ጠጋኝነትና የደህንነት ጥበቃ ትምህርቶች እንደሚሰጡበት ዶክተር ጌታቸው ገልፀዋል።

ትምህርቱን ለመስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ ሃገሪቱ በአቭየሽኑ ዘርፍ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ትምህርት እንደምትሰጠው ሁሉ በባቡሩ ዘርፍም መሰል ተግባር እንድትከውን ያስችላታል ነው ያሉት።

አብዛኛዎቹ የባቡር ትራንስፖርት የሚጠቀሙ የአፍሪካ ሀገራት ባለሞያዎቻቸውን የሚያሰለጥኑት በደቡብ አፍሪካ ወይም ቻይና በሚገኙ ተቋማት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፥ በአዲስ አበባ የሚቋቋመው የባቡር ትምህርት ማእከል ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አማራጭ እንደሚሆንም ነው ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት።