126ኛው የአድዋ በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል በመላው ሀገራችን የተከበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት በብራስልስ በሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ አስተባባሪነት ቤልጂየም፣ ሉግዘምበርግና ኔዘርላንድስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ተከብሯል፡፡ ውይይቱ በበይነ መረብ የተደረገ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውበታል፡፡ በመድረኩ በቤልጂየም ባለሙሉ ስልጣን ክብርት አምባሳደር ሂሩት ዘመነ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዋነኛነት የአድዋ በዓል በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች የነጻነት ፋና ያበሰረ እንደነበር እና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት እንደሆነ አንስተዋል። በማስከተልም የአድዋ በዓል በመስዋዕትነት አገራችን ተከብራ እንድትቆም ያደረገ ክስተት መሆኑንና አሁንም በዚህ ትውልድ እየተገነባ ያለው የሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ አድዋ መሆኑንና በአንድነት እስከቆምን ድረስ ምንም ነገር ለመስራት የሚያግደን ጉዳይ እንደሌለ ያስመሰከርንበትና በቀጣይ ልማታችንን ለማሳካት ተባብረን መስራት እንዳለብን አስገንዝበዋል፡፡
በመቀጠል በየአገሩ የተወከሉት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከቤልጂየም አቶ ዮሐንስ ዘርፉ፣ ከኔዘርላንድስ ወ/ሮ ማህሌት አየለ እና ከሉግዘምበርግ አቶ አዘዘ ከበደ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ቀጥሎም በኤምባሲው የተዘጋጀ የአድዋን በዓል የሚዘክር አጭር የዶክመንታሪ ፊልም የታየ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራ ክፍል በአቶ በሪሁ ደጉ ስለአድዋ በዓል ታሪክ የሚዘክር ገለጻ አድርገዋል፡፡ በማስከተል ተሳታፊዎች ስለበዓሉ ያላቸውን አስተያየት በውይይቱ አንስተዋል፡፡
በቀረቡት መልዕክቶችና ገለጻዎች አድዋ ዓለምን ከቀየሩ ታሪካዊ ክስተቶች አንዱ እንደሆነ፣ የጥቁር ሕዝቦችና በኮሎኒያሊዝም ስር ወድቀው የነበሩ ሕዝቦች ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች እንደሚላቀቁ የጠቆመ የነጻነት ቀንዲል እንደሆነና የቅኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረ እንደሆነ ተገልጿል።
በተሳታፊዎች በኩልም የአድዋ በአል ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና ጾታ ሣይለዩ በአንድነት በመቆም ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በታላቅ መስዋትዕነት ያመጡት ድል መሆኑን፤ የአሁኑም ትውልድ ስለአድዋ በዓል በትምህርት ካሪኩለም ተካቶ ሊማርበት እንደሚገባ እንዲሁም በጋራ በመቆም ግድቡን የዳግማዊ አድዋ ተምሳሌትነት በማረጋገጥ ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት፤ በአሁኑ ጊዜ እየታዮ ያሉ ልዩነቶች ሊቆሙና በጋራ አገራችንን ማልማትና ወደ ብልፅግና መውሰድ የሁላችንም አደራ መሆኑ አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም የሚቀጥለው የአድዋ በዓል አከባበርን በጎላ መልኩ ለማክበር እንዲቻልና ሌሎች የአፍሪካ አገራትን ባካተተ መልኩ እንዲሆን ስምምነት ተደርሷል፡፡ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ክብርት አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ዲያስፖራው ለአገሩ እያደረገ ያለው መጠነ ሰፊ ድጋፍ በቋሚነት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።