የዐድዋ ድል በዓል “ዐድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል ቤኔሉክስ አገራት የሚኖሩ ኢትዮዽያዊያን፣ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የሚሲዮኑ ባልደረቦች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት ተከብሯል:: በበዓሉ ላይም ክብርት አምባሳደር ሂሩት ዘመነ በዓሉ ለኢትዮዽያዊያን የተለየ ትርጉም ያለው መሆኑን፣የዐድዋ በዓል ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ዓርማ ፋና ወጊ መሆኑን: በዐድዋ ኢትዮጵያዊያን የተጠቀሙበት የጦር ስልትና በአጭር ጊዜ ጦርነቱ መጠናቀቁ ለዘመናዊ የጦር ሳይንስ መማሪያ ሊሆን የሚያስችል እንደሆነና ከሁሉም በላይ ለዐድዋ ድል መገኘት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎና የሕብረብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበት እንደነበረ ገልፀዋል:: አዲሱ ትውልድም የአባቶቹን አደራ ማስቀጠልና የራሱንም አሻራ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
በማስከተልም አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ ስለ ዐድዋ ታሪካዊ ዳራ በሠፊው ገለፃ አድርገዋል:: በመቀጠል ቤልጂየም በሚገኘዉ በአንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ የPhD ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ሽመልስ አየለ ዐድዋ ኢትዬጵያ ገፅታ የቀየረ በሚል መነሻ ከዐድዋ ጦርነት በፊት እና በኃላ በውጭው ዓለም ስለነበራት ገፅታ በማነፃፀር አቅርበዋል:: ድሉ በእርግጥም የጥቁሮች ህዝቦች የነፃነትና የፍትህ ጥያቄን በዓለም ለማስተጋባት ለሚደረገው እንቅስቃሴ መሠረት እንደጣለ ገልፀዋል።
የቤልጂየምና የኔዘርላንድስ ኮሚዩኒቲ አመራር አባላትም በዓሉን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትና ንግግር ያደረጉ ሲሆን ፥ በመጨረሻም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዳቦ በመቁረስና ሻማ በመለኮስ እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶቹ ቀደም ሲል እየታየ የነበረውን የሥዕል ኤግዚቢሽን እንዲጎበኙ በማድረግ የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል።