በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በቤኔሉክስ ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ጋር 129ኛውን የአድዋ ድል በዓል አከበሩ

በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በቤኔሉክስ ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ጋር 129ኛውን የአድዋ ድል በዓል አከበሩ
በቤኔሉክስ አገሮች እና በአውሮፓ ህብረት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አምባሳደርና ዲፕሎማቶች ቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጋር 129ኛውን የአድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት አክብረዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የቤኔሉክስ አገራት እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር እሸቴ ጥላሁን አድዋ ለጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት በመሆን ነፃ ለመውጣት በተካሄዱ ትግሎች መነቃቃት የፈጠረ ታላቅ ድል መሆኑን አስታውሰው፣ የዛሬው ትውልድ እንደ አድዋ የታላቁን ህዳሴ ግድብና ሌሎችም የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክቶችን እና የሀገር መለያ ምልክቶችን በመገንባት የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ማድረግ እንዳለበት፣ ሉዓላዊነትን እና ብሄራዊ ክብርን የማስጠበቅ ኃላፊነት በምንም ዓይነት ፈተና ወይም የፖለቲካ ፍላጎት ለድርድር እንደማይቀርብ ገልፀዋል።
በዓሉን የታደሙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአድዋ ድል የዓለምን የጦርነትና የአሸናፊነት ታሪክ የቀየረ መሆኑን፣ አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩትን ነፃነትና ክብር አስቀጥሎ መሄድ እንደሚገባ፣ ትውልዱ የህዳሴውን ግድብ በማጠናቀቅ ድህነትን ማሸነፍና ለአፍሪካውያን ብሎም ለጥቁር ህዝብ የልማት ተምሳሌት መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
በዓሉ የአገራችን ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር የተጀመረ ሲሆን፣ ስለታላቁ የአድዋ ድል የሚያትት መነሻ ጽሁፍ ለበዓሉ ታዳሚዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመነሻ ጽሑፉ የዓድዋ ድል የአያቶችን የዓላማ ፅናት እና አትንኩኝ ባይነት የታየበት፣ የውስጥ ልዩነቶችን በመቀነስ የውጭ ጠላትን በጋራ ድል በማድረግ መስዋእትነት የተከፈለበት እንደሆን ተገልጿል። በጀግንነትና በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ የጋራ ድል መሆኑ ተወስቷል። ድሉን የሚዘክር ግጥምና ሽለላ በሁለት ሴት የዳያስፖራ አባላት ቀርቧል። ሁለት አንጋፋ የዳያስፖራ አባላት ደግሞ አድዋ ከነተጽእኖ አድራሽነቱ መከበር ያለበት የጥቁር ህዝቦች ድል እንደሆነ አስረድተዋል።
በመቀጠል ለበዓሉ የተዘጋጀውን ኬክ በመቁረስ ፣ የባህላዊ ምግቦች እና የቡና መስተንግዶ ተከናውኖ በዓሉ በቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በተጀመረበት ሁኔታ በድምቀት ተጠናቅቋል።