18ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በድምቀት ተከበረ፣
_________________________________________________________________
በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ባልደረቦች በአገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ “ሰንደቅ አላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ብስራት፣ ለብሄራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ’’ በሚል መሪ ቃል የሰንደቅ አላማ ቀን ዛሬ ጥቅምት 03 ቀን 2018 ዓ.ም. በድምቀት አክብረዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በበዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ለሰንደቅ ዓላማ የሚሰጥ ክብርና ፍቅር፣ ሀገራዊ አንድነትና ህብረብሄራዊነት ለማፅናት በኢትዮጵያውያን የተከፈለውን መስዋዕትነት ማዕከል ማድረግ እንዳለበት ገልፀዋል። አገራችንን እና ሕዝቦቿ በየወቅቱ ያጋጠማቸውን ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን በመሻገር የተመዘገቡ ድሎችን በየዘመኑ መድገምና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስቀጠል የሁሉም ዜጎች ግዴታ እንደሆነ አስረድተዋል።
ስለሰንደቅ አላማችን ክብር ስናስብ የሰላምና ፀጥታ አስከባሪዎች በተለይም የመከላከያ ሰራዊታችንን መስዋዕትነት ከፍ አድርገን ማክበር እንዳለብን አመልክተዋል።የሰንደቅ አላማ ክብር ትውልድና አፅናፋትን ተሻጋሪ ሊሆን እንደሚገባም ገልፀዋል።
እለቱን በማስመልከት የተዘጋጀ ገለፃ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
