በቤኔሉክስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ቀንን በድምቀት አከበሩ

በቤኔሉክስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ቀንን በድምቀት አከበሩ
ብራሰልስ፣ 31 ሜይ 2025- በብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የኢትዮጵያውያን ቀን በአል በቤኔሉክስ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ እና ሉክሰምበርግ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን ለመፍጠር ወሳኝ መድረክ ሆኗል።
በበዓሉ በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አምባሳደር ክቡር እሸቴ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት ያለምንም የውጭ ዕርዳታም ሆነ ብድር፣ በራስ አቅም፣ ህዝባችንን በማስተባበር የተገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተፈጥሮ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን ማንም ሊገፈን እንደማይችል ያረጋገጥንበት፣ አንድነትን፣ ፅናትን፣ የኢኮኖሚ ነፃነትን፣ በራስ መተማመን እና ለመስራት መቻልን የተማርንበት ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልፀዋል። የGERD ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ በቤኔሉክስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ በማመስገን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ ዳያስፖራው በቦንድ ግዢና በስጦታ በመሳተፍ ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በዝግጅቱ አምባሳደር እሸቴ በቤኔሉክስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አመራሮች እና ግለሰቦች አገራዊ የልማት ግቦች በመደገፍ እና ለGERD በቦንድ ግዥ እና በስጦታ በንቃት በመደገፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።
ዳያስፖራው ለግድቡ መጠናቀቅ በቦንድ ግዥ፣ በስጦታ እንዲሁም በገቢ ማሰባሰቢያ ሁነቶች የኢትዮጰያ ቀንን ያከበረ ሲሆን የባህል ሙዚቃ፣ የዳቦ ቆረሳና የኢትዮጰያ ቡና በድምቀት ታይተውበታል። ዝግጅቱ የአንድነት መንፈስን የተላበሰ እና ሀገራዊ ኩራትን ያጎናፀፈ ሲሆን በቤኔሉክስ በሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ያሳየ ሆኗል።