በቤኔሉክስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ልጆች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር ለማነቃቃት እንዲሁም ባህልና እሴትን እንዲያውቁ ለማድረግ ያለመ ከእለታት አንድ ቀን……. በኢትዮጵያ ቤት ልዩ የልጆች መዝናኛ ዝግጅት ብራሰልስ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ዛሬ ነሐሴ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በድምቀት ተከናውኗል።
በዝግጅቱ ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት ልጆች ከምንጫቸው ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ወላጆች ሚና እንዳላቸው አንስተው፣ ዳያስፖራው በሚገኝበት ማህበረሰብ እርስበርስ መተዋወቅ፣ መተሳሰር እንዲሁም ለአገር አንድነት በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በሉግዘምበርግ የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል እና የላሜ ቦራ (ፈረንሳይኛ) ጸሃፊ ማዳም ሄኖኬ ወልደመድህን ኩርት በዝግጅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ዳያስፖራው ለልጆች የኢትዮጵያን ባህልና እሴት በማስተማር ማሳወቅ እንዳለበትና የበለጸገ ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ መኩራት እንደሚገባ ገልፀዋል። ከአገራችን እውቅ የልጆች ታሪኮች አንዱ የሆነውን ” ላሜ ቦራ” የተረት መፅሃፍ በፈረንሳይኛ የፃፉበትን መሰረት ሃሳብ በማብራራት ታሪኩ አንብበዋል።
በቤልጅየም ለማህበራዊ አገልግሎት የመጡት አርቲስት ንብረት ገላው ( እከ) በዝግጅቱ በመገኘት ስለ አገር ፍቅርና በጋራ ስለመስራት አስፈላጊነት ንግግር አድርገዋል። በዝግጅቱ ከተገኙ ልጆች ጋር የቡሄ ጭፈራን እንዲሁም ሌሎች ባህላዊ ጨዋታዎችን በማስተዋወቅ ታዳሚ ልጆች ባህሉን እንዲረዱ አድርገዋል።
በእለቱ ከተረት ንባብ በተጨማሪ ልጆች የራሳቸውን ሃሳብ የሚያመነጩ የሥነ-ጥበብ ስራዎችን እንዲለማመዱ ትስስር እንዲፈጥሩ ተደርጓል።
