የኅብር ቀን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃትን ምክንያት በማድረግ ደማቅ ፕሮግራም ተካሄደ፣
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃት እና የ2018 ዓ.ም. የአገራችን የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ጳጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ.ም. (የኅብር ቀን) ጥልቅ የደስታ ስሜት የተንጸባረቀበት በዓል ተከብሯል። በበዓሉ ላይ በቤልጅዬም፣ በኔዘርላንደስ እና በሉግዘምበርግ የሚኖሩ ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ታድመዋል። በዓሉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ አባቶች፣ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን መሪዎች እና በብራሰልስ የኢትዮጵያ ሙስሊም ኮሙዩኒቲ የሃይማኖት አባት በጸሎት አስጀምረዋል።
ለግድቡ ግንባታ በሙያቸውና በአስተባባሪነት ያገለገሉ ግለሰቦች እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ገቢ ተሰባስቧል። ለግድቡ እና ለሀገር ጥብቅና በመቆም ለጋራ የድል ቀን የታገሉ ምስጋና ቀርቦላቸዋል። የህዳሴ ግድብና የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት መግለጫ ከኤምባሲው ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። የግድቡን መጠናቀቅ የሚዘክር ግጥም እንዲሁም ከብራሰልስ የአፋር ኮሙዩኒቲ በእጅጉ የተደነቀ ባህላዊ ጨዋታ ቀርቧል።
ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን 2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ህዝብ ጉስቁልና ማብቂያና የብልጽግና ጉዞ መሰረቱ የሚፀናበት ዓመት መጀመሪያ እንደሚሆን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በብዙ ቋንቋ፣ ባህል፣ እሴት እና ሃይማኖት ያሸበረቀች አገር ናትም ብለዋል። ብዝሃነታችን እና የአባቶቻችን የድል ገድሎች ፈጣሪ ካደለን ውብ አገራዊ የተፈጥሮ ገፀ-በረከቶች ጋር ተዳምረው የድንቅና ጥልቅ ታሪክ አገር ባለቤቶች እንድንሆን አድርጎናል ሲሉም በአንክሮ ገልጸዋል። አንድነታችን በጋራ መስዋዕትነት የተገኘ ስለሆነ ያኮራናል በማለትም ድል ያለ ዋጋ እንደማይገኝ አስገንዝበዋል። ብዝኃነታችን ውበታችን እና ታሪካችን የተገመደበት ሰበዝ በመሆኑ፣ ይህንን ሃብት የምናደምቀው “ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” ነው በሚለው መርህ ነው ሲሉም አስምረዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ በመዘግየትና ተስፋ በሚያስቆረጥ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት፣ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋርጠውበት ለውድቀት ከተቃረበበት ሁኔታ በማውጣት በተለየ ቁርጠኝነትና ክትትል ለውጤት በመብቃቱ ለክቡር ዶ/ር ዐብይ አህመድና አብረዋቸው ለሰሩ ዜጎች አምባሳደር አሸቴ ምስጋና አቅርበዋል። ከለውጡ በኋላ ዶ/ር ዐብይ የሰጡት የህይወት ዋጋዎችን የጠየቀ ቆራጥ አመራር በትውልዶች የጀግንነት ታሪክ ሲወሳ ይኖራልም ብለዋል። መሪአችን የህዳሴ ግድብ በፍጥነትና በከፍተኛ ጥራት እንዲጠናቀቅ በተጫወቱት ቁልፍ ሚና እና መላው ኢትዮጵያዊ በአንድነት ተሰልፎ ባደረገው ርብብር የአሁኑ ደማቅ ታሪክ ተፅፏል ካሉ በኋላ፣ ግድቡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የዚህ ትውልድ ዳግማዊ አድዋ ሆኖ ይዘከራል ብለዋል። በቀጣይ ለምንሰራቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች የፅናት እና የስራ ጥራት ምሳሌ ሆኖ ያገለግለናል፣ ለዚህ ድል አምላካችንን እንደገና እናመስግነው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።