የ2018 ዓ.ም. መስቀል ደመራ በዓል በብራሰልስ በድምቀት ተከበረ፣
የመስቀል ደመራ በዓል በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ደብረ- ምህረት ቅድስት ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ በብራሰልስ የአ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ባልደረቦች የተገኙ ሲሆን ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በዓሉን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸው መስቀል በዩኔስኮ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡንና የሁሉም የሰው ልጆች ቅርስ መሆኑን አንስተው የበዓሉ መሰረት ህዝባዊ ትብብር፣ አንድነትና የእምነት ጥንካሬ በመሆኑ ግዙፉን የደመራ ነበልባል ለመፍጠር ሁሉም የራሱን የበራ ችቦ በአንድ ላይ እንደሚዳምር ሁሉ ለኢትዮጵያችን ልዕልና፣ ሰላም፣ ልማትና ብሩህ ተስፋ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክትና ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርበዋል።
የWoluwe Saint Pierre Commune Premier Echievien, Mr. Tanguy Verheyen በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ብራስልስ የብዝሐነት ተቀባይ አገር መሆኗን አንስተው፣ በየዓመቱ የሚከበረው የመስቀል በዓል ተካፋይ በመሆናቸው ደስታቸውንና መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በበዓሉ የሀይማኖት አባቶች መልአከ ስብሐት አባ ገ/ኪዳን እንየው(ቆሞስ) የቤልጅየም አንትወርፕ ደብር ስብሐት ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣ መላከብርሃን ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል የሮተርዳም ደብረ መዊዕ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ፣ ሊቀ ጉባዔ መሪገታ ጽጌ የኮርትሬክ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ እና ቀሲስ አክሊሉ ወርቁ የብራስልስ ደብረ ምህረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
