በቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ፤
በቤኔሉክስ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ጋር የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ ድርሻና ዕድሎች፣ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንዲሁም ወቅታዊ አገራዊ የሰላም ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ፌብሩዋሪ 07 ቀን 2026 ዓ.ም. ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ክቡር አምባሳደር አንተነህ ታሪኩ እና ክቡር አምባሳደር መርዋን በድሪ በክብር እንግድነት ተገኝተው ከታዳሚዎች ጋር ሃሳብ ተለዋውጠዋል። በክቡር አምባሳደር አንተነህ እና በኤምባሲው ሲኒየር ዲፕሎማት አማካኝነት፤ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በዕውቀት ሽግግር ዙሪያ ያሉ ሰፊ ዕድሎችና መንግስት ያዘጋጃቸው ማበረታቻዎች (Incentives) ላይ ዝርዝር ገለፃ ቀርቧል። ክቡር አምባሳደር አንተነህ በቅርብ ዓመታት የተካሄዱ የማይክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን በስፋት በማብራራት፣ በቤኔሉክስ አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ያላቸውን አቅም በማቀናጀት በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ድርሻውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል። ክቡር የሚሲዮኑ መሪ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በበኩላቸው ኤምባሲው የዳያስፖራ ልማት ተሳትፎን ለማገዝና ቁርጠኝነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የኢንቨስትመንት ዘርፍ በንቃት በመሰማራት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኤምባሲው የሚዘጋጁት ወርሃዊ ስብሰባዎች እጅግ አስተማሪና ከሚሲዮኑ ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ መሰል መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። በመጨረሻም በኢንቨስትመንትና በልማት ስራዎች ላይ የሚገጥሙ ማነቆዎችን በመለየት፣ ተግባራዊና ዘላቂ መፍትሄዎችን በጋራ ለመታገል በመግባባት ስብሰባው ተጠናቅቋል።




