በቤኔሉክስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ቀንን በድምቀት አከበሩ

በቤኔሉክስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ቀንን በድምቀት አከበሩ
ብራሰልስ፣ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም. – ብራስልስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የክቡር አምባሳደሩ መኖሪያ ቤት የኢትዮጵያውያን ቀን በቤኔሉክስ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር በድምቀት ተከብሯል። ፕሮግራሙ በሃይማኖት አባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን ኩነቱ በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ እና ሉክሰምበርግ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ የሚዘመርበት የአብሮነት፣ የማንነት እና የባህል ስንቅ መድረክ ሆኗል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አምባሳደር ክቡር እሸቴ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት የባህር በርና የወደብ ባለቤትነት መብትን ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያን ከድህነት አውጥቶ የማይናወጥ የስልጣኔ መሰረትን እንደገና ለመጣልና ለማጽናት ያለመ ብሄራዊ ራዕይ በመሆኑ በመተሳሰብና በመተባበር ልናሳካው እንደሚገባ ገልፀዋል።
በሁሉም ዘርፍ ሉዓላዊነታችንን በማረጋገጥ ወገኝተኝነታችንን ለሀገር ግንባታና ለአገራችን የነገ ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት አመልክተዋል። ዳያስፖራው በእውቀትና በሀብት ለአገር ልማት የበኩሉን በየዘርፉ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
በዝግጅቱ ሂደት ለበጎ አድራጎት የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም፣ ልዩ ልዩ የዳያስፖራውን ማህበራዊ ግንኙነትና ትስስር የሚያጠናክሩ የልጆችና አዋቂዎች የመዝናኛ ፕሮግራሞችና ውድድሮች ተከናውነዋል። የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ፣ የቡና ስነ-ስርዓት፣ ሙዚቃ እዲሁም ለበዓሉ ድምቀት የተዘጋጀውን ዳቦና ኬክ በመቁረስ ኢትዮጵያዊነት በድምቀት ሲዘከር ውሏል።