ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የ2ዐ19 የሠላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን በማስመልከት ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት መልዕክት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የ2ዐ19 የሠላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን በማስመልከት ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ያስተላለፉት መልዕክት

በግለሰብም ሆነ በአንድ አገር ሕይወት ውስጥ የተለየ ቦታ የሚይዙ ቀኖች አሉ፡፡ የዛሬው ቀን ከእነዚህ መካከል አንደኛው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፡፡
በቅድሚያ በአገራችንና በውጭ አገራት በሚገኙ መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም በራሴ ስም እንኳን ደስ አሎት ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅርን ከማቀንቀን አቋርጠው አያውቁም፡፡ በሀገር ውስጥ የነበረውን አስፈሪ የፖለቲካ ፍጥጫ በማርገብ፣ በውጭ ሀገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ በማድረግ፣ ያለፈውን ታሪክ ዕሴቶች አስጠብቀን፣ ስህተቶችንም አርመን፣ አዳዲስ ዕሴቶችን በመጨመር የምንሄድበትን አካሄድ በመንደፍ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውንና ሁለት አሥርተ ዓመታት ያስቆጠረውን ውጥረት በሠላም በመፍታት፣ ትላንት የተመረቀውን የአንድነት ፓርክ ዓይነት ያሉ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ወደፊት ሊወስዱ የሚችሉ አሻራዎችን ለትውልድ በመተው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ትብብርን በማበረታታት፣ በጎረቤት ሀገሮችና በአገሮች መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያውን በመውሰድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ በአጭር ጊዜ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡
ዛሬ የተሸለሙት የኖቤል የሰላም ሽልማት ዋና ትርጉሙ ለእነዚህ ታላላቅ ሥራዎቻቸው ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና መሰጠቱ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ኢትዮጵያ ላይ ያለውንም ተስፋ ያመላከተ ነው፡፡ ከሁሉም መአዘን እያስተጋባ ያለው የደስታ ስሜት እኛ ኢትዮጵያዊያን አንገታችንን በኩራት ከፍ እንድናደርግ የሚጋብዘን ነው፡፡ በእውነትም ልንኮራበት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነንና ተባብረን ሠርተን ያልተሳካልን ጊዜ የለም፡፡ ፉክክራችንን እርስ በርስ ማድረጋችንን ትተን ከዓለም ጋር ካደረግነው ማሸነፍ እንደምንችል ታሪክ በተደጋጋሚ ነግሮናል፡፡ አንድ ሆነን ቅኝ ገዥዎችን ታግለን ተሳክቶልናል፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ነጻ እንዲወጡ አብረን ታግለን ተሳክቶልናል፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመሠረት የምንችለው ሁሉ አድርገን ተሳክቶልናል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ታግለን ተሳክቶልናል፤
የምናተርፈው ከመለያየታችን ሳይሆን ከአንድነታችን፣ ከስንፍናችን ሳይሆን ከሥራችን መሆኑን አይተናል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዓለምን የሚያስደንቅ ሥራ ሠርቶ በዓለም መድረክ ላይ መቆም እንደሚቻል የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት አሳይቶናል፡፡
እየተደማመጥን፣ እየተከባበርን የአገራችንን አንድነትና ጥቅም በማስቀደም ከዚህ በላይ ከሠራን ሥልጣኔያችንና ብልጽግናችን ራሱ ይሸልመናል፡፡ ሠላማችንና መረጋጋታችን ራሱ ይሸልመናል፡፡ የኢኮኖሚያችን ዕድገትና ዴሞክራሲያችን መጎልበት ራሱ ይሸልመናል፡፡
ከግራ ከቀኝ የሚወረወረውን እያሳለፉ፣ ፀንቶ መሥራት ምን ዋጋ እንዳለው የዛሬ ሽልማት ይነግረናል፤ እዚህም እዚያም በሚከሠቱ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ሳይታወኩ ወደፊት እያዩ የአገርን ጥቅምና ታላቅነት በማስቀደም መሥራት እንዴት ያለ ክብር እንዳለው የዛሬው ሽልማት ያስተምረናል፡፡
ለኢትዮጵያ ታላቅነት ስንል፤ ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት፣ ባንስማማም እንኳን ላለመስማማት ተስማምተን፣ በትንንሽ ምክንያቶች ሳንደናቀፍ፣ ሀገራችንን ብቻ አስቀድመን በርትተን እንሥራ፡፡ ይህ ከሆነ ከዚህ በላይ ገና ብዙ ድሎች ይቀሩናል፡፡
በድጋሚ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እንኳን ደስ ያለዎት