የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽ/ቤት ሳምንታዊ መደበኛ መግለጫ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽ/ቤት ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም በሊባኖስና ጂቡቲ የሚገኙ ኢትዮጰያውን ዜጎች ጉዳይ፣ በደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንዲሁም በአውሮፓ በተካሄዱ የቢዝነስ ፎረሞችን እና ሌሎችን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የመ/ቤቱ ዋና ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት እ.ኤ.አ ከኦክቶበር 17 ቀን 2019 ጀምሮ በሊባኖስ መዲና እንዲሁም በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ በሚገኘው ሰላማዊ ሰልፍ በዚያው የሚኖሩ ከ400 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በዜጎቻችን ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት የለም ያሉ ሲሆን ቤይሩት የሚገኘው የኢፌዲሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በአሁን ሰዓት በማህበራዊ ሚዲያ (በፌስ ቡክ፣ በድህረ ገጹ ወዘተ) ሁኔታውን አስመልክቶ ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ፣ የሰልፉ ተባባሪ እንዳይሆኑ መልዕክት በማስተላለፍ ስልክ መስመሩን ክፍት አድሮጎ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም በጂቡቲ ታጁራና ኦቦክ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ጤንነታቸውና ክብራቸውን ተጠብቆ ወደ አገራቸው በፍቃደኝነት እንዲመለሱ በጂቡቲ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ከጂቡቲ መንግስት፣ ከክልል መስተዳድሮቹና እና በጂቡቲ ዓለም-አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ለሚዲያ አካላት አብራርተዋል፡፡ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለው ሳዑዲ-አረቢያን መዳረሻቸው ለማድረግ ጂቡቲን አልፈው የመንን ለማቋረጥ ከሚሞክሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ባሳለፍነው ሩብ ዓመት ብቻ (ከሐምሌ-መስከረም) 1221 የሚሆኑ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉንም አቶ ነብያት ገልጸዋል።
ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ እ.ኤ.አ ህዳር 12 ቀን 2019 ይመሰረታል ተብሎ በሚጠበቀው የሽግግር መንግስት ዙሪያ በፈራሚ ሀይሎቹ መካከል የሃሰባ ልዩነቶች እንዳሉ አንስተው የኢጋድ አባል ሃገራት ተሰብስበው በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ አቋም እንደሚይዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሩሲያ/ሶቺ/ በተደረገዉ ውይይት መሰረት የቴክኒክ ዉይይት እንደሚቀጥል ገልጸው በቅርቡ በዋሽንግተን የሚካሄደው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የድርድር ሳይሆን ዉይይት ለማካሄድ ያቀደ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ወደ ተለያዩ ሀገራት መልዕክት ይዞ በመጓዝ የኢትዮጵያን አቋም በሚገባ ለማስረዳት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ መሆኑንም ግልጽ አድርገዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በተመለከተ አገራችን ከጣሊያን እና ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንዲረዳና ከሀገራቱ ጋር ያለውን የቢዝነስ ግንኙነት ለማጠናከር በሮም፣ በሚላንና በፓሪስ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የልኡካን ቡድን የተሳተፈባቸው ሁለት ፎረሞች እ.ኤ.አ ከኦክቶበር 16 -21 /2019 መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በፎረሞቹ ከየሀገራቱ የተወጣጡ ባለሀብቶች መታደማቸውንና በአገራችን እየተካሄደ ባለው ለውጥ ዙሪያ በጣሊያንና በፈረንሳይ ኩባንያዎች በኩል አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት ማድረግ መቻሉንም አስታውሰዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ነብያት ከጋዜጠኞቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።