ዛሬ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቤልጅዬም እና ላክሰምበርግ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ ጋር ውይይት አካሂዷል። በዕለቱ በቤልጅዬም እና ላክሰምበርግ የሚኖሩ ከ110 በላይ የዳየስፖራ ማህበረሰብ አባላት የተገኙ ሲሆን፣ በመድረኩ በሀገራችን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሀገሪቱ የልማት ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እንዲሁም በሚሲዮኑ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በቤልጅዬም፣ ላክሰምባርግ እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ክቡር አምባሳደር ግሩም አባይ ሲሆኑ፣ በንግግራቸው ባለፉት ሁለት አመታት በሃገር ውስጥም ሆነ በክልላዊ ጉዳዮች ዙርያ መንግሰት ዘርፈ ብዙ እና መጠነ ሰፊ የለውጥ ስራዎች ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰው በተለይም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሀገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ብዙ ስራዎች እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም መጪውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ለማካሄድ መንግሰት እየሰራ ያለውን ስራ አብራርተዋል።
በውይይቱ መድረኩ የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አቶ ገብረሚካኤል ገብረጻዲቅ ዳያስፖራው በኢትዮጰያ ሊሳተፍባቸው በሚችልባቸው የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በመጨረሻም ከተሳታፊዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች በክቡር አምባሳደር ግሩም አባይ ማብራሪያ በመሰጠት መድረኩ ተጠናቋል።