በቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትጵያውያን ጋር የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ፡፡

በቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትጵያውያን ጋር የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ፡፡
========================
በቤኔሉክስ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትጵያውያን ጋር በአገራችን ወቅታዊና የፖለቲካ አጀንዳዎች፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍና የቦንድ ግዢ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል። የውይይት መድረኩን ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን የመሩት ሲሆን፤ በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሃብት ማሰባሰብ እንዲቀጥልና ሁሉም የበኩሉን አሻራ እንዲያኖር ጠይቀዋል፡፡ መቻቻል ለኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ለውጥ፣ ልማድ እና ሪፎርም በተሰኙ ሁለት ርእሶችም ሰፊ ገለጻ እና ውይይት ተደርጓል፡፡ ሦስት የጽሁፍ አቅራቢዎች በየርእሶቹ የመወያያ መሪ ሃሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሰብሳቢዎች የሚሰማቸውን ደጋፊና የተለዩ ነጥቦች በማንሳት አስተያየታቸውን አሰምተዋል፡፡
በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፣ በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ለመላው አፍሪካ መነቃቃትን የፈጠረ፣ የውጭ አገር መንግሥታትና ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ሳይኖር በራስ አቅም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚቻል በመላው አፍሪካ ሞዴል የሚሆን ሥራ እንደተከናወነ ተገልጿል፡፡ በስብሰባው የተገኙ ታዳሚዎች በቦንድ ግዢ እና በስጦታ እንዲሳተፉና ቃልም እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ ዲስፖራው የአገራዊ ልማት ተሳትፎን በማሳደግ፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ሃሳብ በመስጠትና በሰላማዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ለማድረግ እና ለተሻለ ውጤት በጋራ ለመስራት መልእክት ተላልፋል፡፡