ሃያኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ በድምቀት ተከበረ፤
ሃያኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በብራሰልስ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ በቤኔሉክስ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በድምቀት ተከብሯል። በዓሉን የሃይማኖት አባቶች በጸሎተ ቡራኬ አስጀምረዋል። የሃይማኖት አባቶች ለሀገራችን ሰላም፣ ለህዝቧ አንድነትና ብልጽግና መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።
በዓሉን በማስመልከት ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት በበርካታ ስኬቶች ታጅቦ የሚከበረው የዘንድሮው በዓል የመተሳሰብ፣ የመግባባትና አንድነትን የማጠናክር አጀንዳን ቀዳሚ ብሔራዊ ጉዳያችን በማድረግ ነው ብለዋል። ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ኢትዮጵያ በማጎልበት ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅብን ገልፀዋል።
የአገራችን ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ እና ያላቸውን እምቅ የባህል እና ቁሳዊ ሀብት እንዲጠቀሙ ተግቶ መስራት እንደሚገባ፣ ለብሔራዊ አጀንዳዎቻችን በጋራ በመቆም የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር አስፈላጊ እንደሆነ አስምረውበታል። ኢትዮጵያ ዋስትናው የተረጋገጠ የባህር በር እንዲኖራት ለማድረግ ሰላማዊ እና በትብብር ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ትግል ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ በአንድነት ለዚሁ እንድንቆም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የበዓሉን ዓላማ የሚያስገነዝብ ሰነድ በኤምባሲው ከፍተኛ የፖለቲካ ባለሙያ አቶ ኦብሳ ተሰማ ቀርቦ በታዳሚዎች ውይይት ተደርጎበታል።
በዓሉን በማስመልከት ብራሰልስ የሚገኘው የአፋር ኮሚኒቲ ተወካዮች ባህላዊ ሙዚቃና ጭፈራ አቅርበዋል። የሶማሌ ኮሚኒቲ አባላት ባህላዊ ጭፈራ ያቀረቡ ሲሆን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙዚቃ፣ የኬክና ዳቦ ቆረሳ፣ ባህላዊ ምግብ እንዲሁም የቡና ስነ-ሥርዓት ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥተውታል።




