የኢትዮጵያ እና ቤልጅየም 120ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ክብረ- በዓል በብራሰልስ ተከበረ፤

የኢትዮጵያ እና ቤልጅየም 120ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ክብረ- በዓል በብራሰልስ ተከበረ፤
ብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቤልጅየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ እና በቤልጂየም መንግሥታት መካከል መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተጀመረበትን 120ኛ አመት በዓል Press Club Brussels Europe በተባለው ማዕከል ሜይ 28 ቀን 2026 ዓ.ም. አክብሯል። እ.ኤ.አ. 2026 ዓ.ም. ግንኙነቱን ለመዘከር ከሚዘጋጁ ተከታታይ ሁነቶች የመጀመሪያ የሆነው “Images of Friendship: 120” የፎቶ ኤግዚቢሽን በእለቱ ተከፍቷል።
በቤልጅየም የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በመክፈቻ ንግግራቸው በኢትዮጵያ እና በቤልጂየም መካከል ያለውን ጥልቅና ታሪካዊ ትስስር በማንሳት ከመደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገር በንግድ፣ በባህል፣ በትምህርት ትብብር እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የቤልጅየም አምባሳደር H.E. Annelies Verstichel በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የአጋርነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
የእለቱ የክብር እንግዳ የቤልጂየም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ፣ የአውሮፓ ጉዳዮች እና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስትር የካቢኔ ኃላፊ H.E. Hubert Roisin በዓሉን በማስመልከት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ቤልጂየም በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብሮች ለማጠናከር እንደሚሰራ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ እንዲሁም የፕሮቶኮል ሹሙ ተገኝተዋል።
በዝግጅቱ Mr. Tim Ianna በተባሉ ግለሰብ “The Tale of Two Lions” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የኢትዮ-ቤልጂየም ታሪካዊ ግንኙነቶች የሚዘክር ጽሁፍ አቅርበዋል። በመቀጠልም በግንኙነቱ ዋና ዋና የነበሩ ኦፊሴላዊ ጉብኝቶችን እና ሁነቶችን የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርቧል።
የእለቱ ድምቀት የነበረው “Images of Friendship: 120” የተሰኘ በኢትዮጵያና በቤልጂየም መካከል ያለውን አጋርነትና ግንኙነት የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በክብር እንግዳው እና በሚሲዮናችን መሪ ተከፍቶ በበዓሉ ታዳሚዎች ተጎብኝቷል።