በቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ስለ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች የውይይት መድረክ ተካሄደ

በቤኔሉክስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ስለ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች የውይይት መድረክ ተካሄደ
=====================
በቤኔሉክስ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች፣ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክረ-ሃሳብ እና የ2018 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫን ተከትሎ ስለተከናወነው የመንግሥት ምስረታን በሚመለት ወርሃዊ የበይነ መረብ ውይይት ኦክቶበር 10 ቀን 2026 ዓ.ም. ተካሂዷል።
የውይይቱ ዓላማ ዳያስፖራው ስለ አገራዊ ጉዳዮች ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝና ያለውን ግንዛቤም ለማጎልበት፣ በተለይ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ሃሳብ ለመለዋወጥ ብሎም በአገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማጠናከር ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክቡር የሚሲዮኑ መሪ አምባሳደር እሸቴ ቀደም ባሉ አመታት እንዲሁም በአገራዊ ምክክር ሂደት ዳያስፖራው ላበረከተው አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበው፣ የሀገራዊ ምክክሩ ውጤት የመላው ኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር ወደ በለጠ አሳታፊ አቅጣጫ እንደሚመራው ገልጸዋል። አክለውም የ2018ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ፣ የምክክሩ ውጤታማነት፣ የመንግሥት ምስረታ ሂደት እና ሰሞኑን የትግራይ ሕዝብ ለሁነቶች ያሳየው ምላሽ የሀገራችንን የዲሞክራሲ ጉዞ ብሩህነት የሚያጎላ መሆኑን አብራርተዋል። የሰባት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን ዋጋ ያስከፈለ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማብቂያ ላይ እንገኛለን፣ ስልጣን ከሕዝብ ምርጫ ውጭ መጠበቅ አበቃ በማለት በአትኩሮት ገልጸዋል። አምባሳደሩ ሁሉም የዳያስፖራ አባል ለሀገር እድገት፣ ለሰላም እና ለልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
በማስከተል ክቡር የሚሲዮኑ ምክትል መሪ አቶ ሰሙንጉስ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች፣ በመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችና በመንግሥት ምስረታ ሂደት ላይ ዝርዝር ገለጻ ( Presentation) አቅርበዋል። በገለጻቸውም ሰላምን ማስፈን፣ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር፣ የአገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑ አብራርተዋል።
በተለይም የፖለቲካ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በውይይትና በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት ቅድሚያ መስጠት ባህል ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። የአገርን የረጅም ጊዜ ጥቅም ከዕለታዊ የፖለቲካ አጀንዳዎች በላይ በማስቀደም፣ ዘላቂ ሰላምን፣ የኢኮኖሚ ልማትንና የብሔራዊ ጥቅም ጥበቃን ያማከለ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ መከተል አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በጋራ እንዲቆሙና ለሰላምና ለመረጋጋት የሚያግዙ ተግባራትን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ የውስጥም ሆነ የውጭ አካላትን ተግባራት አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። ለአገር መከላከያ ሰራዊትም ያላቸውን ክብርና ድጋፍ አረጋግጠዋል።
ተሳታፊዎቹ የአገርን አንድነት የሚጎዱ የሐሰት መረጃዎችን በጋራ በመመከት፣ የአገራቸውን ሰላምና ልማት ማስቀደም እንደሚገባም ያለልዩነት ተናግረዋል። በአገር ውስጥ የሰላም ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርና ፍትህ እንዲስፋፋ የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ እንደሆኑም ገልጸዋል። በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ የአገርን ሰላምና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ፣ ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከርና ለዘላቂ ልማት የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ከሚሲዮኑ ጋር እንደሚሰሩ ገልጸው ውይይቱ ተጠናቅቋል።